top of page

ዜና

ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በላስ ቬጋስ ደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፲፯ ዓ/ም ለ ፲፬ ደቀ መዛሙርት ሢመተ ዲቁና ሰጡ።

ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በላስ ቬጋስ ደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፲፯ ዓ/ም ለ ፲፬ ደቀ መዛሙርት ሢመተ ዲቁና ያከናወኑ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራት የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን ባርከው አቁርበዋል።
ብጹዕነታቸው በዕለቱ ለወላጆች ባስተላለፉት አባታዊ ቃለ በረከት የክህነት አገልግሎት መመረጥ መሆኑን ፣ ከእግዚአብሔር መሆኑን እና የቅድስና አገልግሎት መሆኑን በመግለጽ ሕዝብን እና እግዚአብሔርን በቅንነት ከማገልገል የበለጠ ምንም ነገር እንደሌለ አመልክተው ወላጆችን እና ደቀ መዛሙርቱን ያስተማሩ ካህናቱን አመስግነዋል።

Read More

የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ፬ኛ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር በተገኙበት ተከናወነ።


የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባውን መስከረም ፲ እና ፲፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ/ም በፍኖተ ሎዛ አቡነ ተ/ኃይማኖት የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሳክራሜንቶ በማካሄድ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሣኔ አሳልፏል የስብሰባ አቋም መግለጫም አውጥቷል።

Read More

የስብሰባ ጥሪ

የስብሰባ ጥሪ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ላሉ የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን አድባራት የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች፤

የስብሰባ ቀን ለውጥ

የሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ ቀን ለውጥ

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ዓመታዊ ንግሥ በዓል በኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ አንድነት ገዳም ዛሬ ሰኔ ፳፱ በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ዓመታዊ ንግሥ በዓል በኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ አንድነት ገዳም ዛሬ ሰኔ ፳፱ በታላቅ ድምቀት ተከበረ። ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና የገዳሙ መስራች ፣ ብጹዕ አቡነ ያዕቆብ የጆርጂያ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የመጡ አበው መነኮሳት ፣ ቀሳውስት ፣ ዲያቆናት ፣ የአድባራት ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምዕመናን ከዋዜማው ጀምሮ ተገኝተው በዓሉን በታላቅ መንፈሣዊ ድምቀት አክብረዋል።
የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ አንድነት ገዳም ለብዙዎች መጽናኛ ፣ የሱባዔ ፣ የፈውስ እና የድኅነት ቅዱስ መካን ኾኖ እያገለገለ ያለ ታላቅ የበረከት ቦታ መሆኑን ለሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ቃላቸውን የሰጡ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ገልጸዋል። በዕለቱም ለዲቁና ማዕረግ ለተዘጋጁ ደቀ መዛሙርት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ዻዻስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር ስለልጣነ ክህነት ሰጥተዋል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A +++++++++++++++++++++++++

Read More

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባዔ በሰሜን ካሊፎርኒያ በሳን ሆዜ መካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ተከበረ ፡፡

በየዓመቱ በበዓለ ሃምሳ /በዓለ ጰራቅሊጦስ/ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በዓል በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ፤ በሰሜን ካሊፎርኒያ ወረዳ በሳን ሆዜ መካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ/ም ተከበረ፡፡ በዕለቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ስብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ በቀጥታ መስመር ተገኝተው ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት ጥቅምና በአሁኑ ጊዜ በፈተና ላይ ስላለችው ቤተ ክርስቲያን ያለውን ዘርፈ ብዙ አስተዋጽዖ በሠፊው የገለጹ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አንድነት ሕብረት ለሀገረ ስብከቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የላቀ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። በመቀጠል የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ሥዩማን ቀሲስ ቡሩክ በቀጥታ መስመር ባስተላለፉት መልዕክት በሀገረ ስብከቱ አድባራት ሥር ያሉ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች አንድነታቸውን ለመጠበቅ እና በመንፈሣዊ የአገልግሎት ዕውቀታቸው ልምድ ለመለዋወጥ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ማዕከል ባደረጉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ለመወያየትና ለመመካከር ቋሚ የሩብ ዓመት ወይም የግማሽ ዓመት ግንኙነት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተጨማሪም የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ተገኑ እንዲሁም የወረዳው ሊቀ ካህናት መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ተመስገን በጉባዔው ተገኝተው በሰንበት ት/ት ቤት አገልግሎት ዙሪያ ሠፊ ምክር እና መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ፤ የዕለቱ ተጋባዥ መምህር እና የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ኀላፊ ቀሲስ አሉላ ዕለቱንና በዓሉን መነሻ በማድረግ “በአንድ ልብ ነበሩ” (ሐዋ 2፡1) በሚል ርዕስ የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮችን አንድነትን የሚመለከት ትምህርት ሠፊ የአገልግሎት ትምህርት ተሰጥቷል። በመጨረሻም በሰሜን ካሊፎርኒያ ወረዳ ቤ/ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካይ መዘምርት ሠናይት አስተባባሪነት ለተደረገው አገልግሎት እና ከመካነ ራማ ቅ/ገብርኤል ሣንሆዜ እንዲሁም ከደብረ ይባቤ ቅ/ገብርኤል ሣንሆዜ አድባራት በቊጥር ልቀው በጉባዔው ለተገኙ የሰንበት ት/ቤት አባላት በሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ምሥጋና የቀረበ ሲኾን በመዝሙር ፤ በጸበል ጸዲቅ ፤ በምክክርና በወይይት እንዲሁም በኅብረት ጸሎት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A

Read More

በዓለ ጰራቅሊጦስ በላስ ቬጋስ ከተማ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል

ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓለ ጰራቅሊጦስን በላስ ቬጋስ ከተማ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል በመገኘት ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ጋር አከበሩ። በዕለቱ ብጹእነታቸው ቀድሰው በማቁረብ ፣ አባታዊ ቃለ በረከት በማስተላለፍ እና ለኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም የጸበል ቤት ማሠሪያ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ በማስተባበር ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽመዋል። “የትንሣኤውን ኃይል ማወቅ” በሚል ኃይለ ቃል ስለ ክርስቶስ ነገረ ትንሣኤ እና ስለ ትንሣኤው ዓላማ ሠፊ ትምህርት የሰጡ ሲኾን ዕለተ ጰራቅሊጦስ የቤተ ክርስቲያን ልደት ፣ ሁላችን በመንፈስ ቅዱስ የታደስንበት ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልን ያገኘንበት ፣ በመንፈስ ቅዱስ ወደ ፊት የምንጓዝበት በመንፈስ ቅዱስ እንደ ሐዋርያት እስከ ሞት ድረስ ራሳችንን ስለ ክርስቶስ አሳልፈን የምንሰጥበት ኃይል የተሰጠበት ዕለት መኾኑን በዓቢይ ቃል አስተምረዋል። በመጨረሻም ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር የነበረ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን ፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ፣ ሀገርን የሚጠብቅ መኾኑን አማኞች እንዲያስተውሉ በማሳሰብ የካቴድራሉ ማህበረ ካህናት እና ምዕመናን ለታላቁ ገዳም የጸበል ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክት በዕለቱ ላደረጉት የገንዘብ አስተዋጽዖ አባታዊ ቃለ በረከት አስተላልፈዋል። ብጹእነታቸው በዚህ ሣምንት የነበራቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት አጠናቀው ምሽቱን ወደ መንበረ ጵጵስናቸው ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም የሚመለሱ ይኾናል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A

Read More

የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ኦክላንድ ካሊፎርኒያ

የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ዛሬ ሰኔ ፲፭ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። ብጹእነታቸው ለዲቁና ማዕረግ ለተዘጋጁ ደቀ መዛሙርት ስልጣነ ክህነት በደብሩ የሰጡ ሲኾን ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራት ቀድሰው በማቁረብ የንግሥ በዓሉ ተከናውኗል። በመጨረሻም ብጹእነታቸው አባታዊ ቃለ በረከት እና ቡራኬ አስተላልፈው የበዓሉ መርሐግብር ተጠናቋል።
ምሽቱን ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር ወደ ላስ ቬጋስ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የሚመለሱ ሲኾን በነገው የጰራቅሊጦስ በዓል በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ላስ ቬጋስ በመገኘት በዓሉን ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ጋር ያከብራሉ።

Read More

የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ላስ ቬጋስ

የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በላስ ቬጋስ ከተማ በሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ላስ ቬጋስ ዛሬ ሰኔ ፲፫ እየተከበረ ይገኛል። የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር ሥርዓተ ቅዳሴውን እየመሩ ቡራኬ የሰጡ ሲኾን ብጹእነታቸው ክብረ በዓሉን እንዳጠናቀቁ ነገ ሰኔ ፲፬ ወደ ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ያቀናሉ። በዚህም የቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ቅዳሜ ሰኔ ፲፭ በኦክላንድ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ብጹእነታቸው በተገኙበት የሚከበር ይኾናል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A
+++++++++++++++++++++++++
ከካቴድራሉ በቀጥታ መስመር የሚተላለፈውን የቀጥታ ሥርጭት ለመከታተል ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ሊንክ ይጠቀሙ https://www.facebook.com/HamereNoahLV

Read More

ሰኔ ፲፪ የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል

ሰኔ ፲፪ የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በላስ ቬጋስ ደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ኃላፊዎች ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ የአድባራት ካህናት ፣ ዲያቆናት ፣ መዘምራን እና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

ከደብሩ በቀጥታ መስመር የሚተላለፍ የክብረ በዓሉን ቀጥታ ስርጭት ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጠቀሙ፦
https://m.facebook.com/stmichaelvegas/

(#CaNvAz Diocese ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም )

የብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳስ ዶ/ር እና የብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር ሐዋርያዊ አገልግሎት በላስ ቬጋስ

የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳስ ዶ/ር እና የብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር በተገኙበት በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ላስ ቬጋስ በታላቅ ድምቀት የተከበረ ሲኾን በቀጣይም ክብረ በዓሉ በላስ ቬጋስ ከተማ በሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ላስ ቬጋስ በነገው ዕለት ይከበራል። ዋዜማው ዛሬ ሰኔ ፲፪ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር እና ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ የኒውዮርክና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ስብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል። በመቀጠል ምሽቱን ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳቱ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ላስ ቬጋስ በመገኘት ካቴድራሉን ጎብኝተዋል በካቴድራሉ የሠርክ ጉባዔ ተገኝተው ቃለ በረከት አስተላልፈዋል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A

Read More

ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ላስ ቬጋስ ከተማ ገቡ።

ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር በነገው ዕለት በላስ ቬጋስ ከተማ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ለሚከበረው የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል ላይ ለመገኘት ፣ በከተማው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ለመባረክ እንዲሁም ምዕመናንን ለማስተማር ዛሬ ከሰዓት ላስ ቬጋስ Harry Reid ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል። መልአከ ሥብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደብሩ አስተዳዳሪ ከደብሩ ካህናት ጋር በመኾን በ Harry Reid ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል። በተመሳሳይ በማለዳ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በዓሉን ለማክበር ላስ ቬጋስ ደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ደብር ደርሰዋል።

ለደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ላስ ቬጋስ ሕንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በአዲስ መልክ በኢትየ‍ኦጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሥነ ሕንጻ ዲዛይን ለሚገነባው የላስ ቬጋስ ደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ አኖሩ።

የዕርገት በዓል

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የዕርገት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

የሀገረ ስብከቱ ሦስተኛ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ

ከነሐሴ ፳፮ እስከ ነሐሴ ፳፯ ፳፻፲፭ ዓ/ም / Sept 1 & 2 2023 በደብረ ሰላም ኢየሱስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኦክላንድ ካሊፎርኒያ የተደረገው የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ስብሰባ መግለጫ፤

ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት በክሊኒካል ሳይኮሎጂ ዶክተር ኦፍ ሳይኮሎጂ ዲግሪ ተመረቁ።

በኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በዛሬው ዕለት October 14 2022 እኤአ ከሰሜን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ የትምህርት ማዕረግ ውጤት (Magna Cum laude) በክሊኒካል ሳይኮሎጂ ዶክተር ኦፍ ሳይኮሎጂ ዲግሪ የተመረቁ ሲኾን በምርቃት መርሐግብሩ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ስብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ ገሰሰ ፣ የሐገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ቡሩክ አልዩ እንዲሁም የአድባራት አስተዳዳሪ ቆሞሳት እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ምእመናን ተገኝተው የእንኳን ደስ አለዎት የደስታ መግለጫቸውን አቅርበዋል። ብጹዕነታቸው በአመራር (leadership) ክህሎታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በተለያየ ከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉ እና እያገለገሉ ያሉ ሲኾን ቤተ ክርስቲያን በፈተና ውስጥ ባለችበት ወቅት በተመደቡበት የአገልግሎት መስክ መንፈስ ቅዱስን በማስቀደም ውጤታማ ሥራ ያስመዘገቡ ናቸው። ከ 20 ዓመት በላይ በምንኲስና ማዕረግ ባገለገሉበት የሎስ አንጀለስ ጽርሀ ጽዮን ቅድስት ማርያም የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል የእንኳን ደስ አለዎት ሠፊ መርሀግብር የተዘጋጀ ሲኾን በዕለቱ ከደብሩ ሰበካ ጉባዔ ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው እና ከደብሩ አገልጋይ ካህናት የእንኳን ደስ አለዎት ገጸ በረከት ተደርጎላቸዋል። በመርሐ ግብሩ የሀገረ ስብከቱ የደስታ መግለጫ እና ገጸ በረከትም የቀረበ ሲኾን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ስብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ ገሰሰ ባስተላለፉት መልዕክት የብጹዕነታቸው ምርቃት የቤተ ክርስቲያን ደስታ ነው ብለዋል። በመቀጠል ክቡር ሥራ አስኪያጁ እንዳስቀመጡት ብጹዕነታቸው በዘመናዊው የትምህርት ዓለም ቆይታቸውም ያሳለፉት ውጣ ውረድ እና ዕውቀታቸውን ከፍ ለማድረግ ያሳዩት ጥረት እና ያስመዘገቡት ውጤት ሀገረ ስብከቱን እና በየደረጃው ያሉ የሀገረ ስብከቱን ኃላፊዎች እንዲሁም የአጥቢያ አገልጋዮችን የሚያበረታታ ነው ብለዋል። ደስታው የቅድስት ቤ/ክርስቲያን ደስታ ስለሆነ ኦርቶዶክሳውያን እንኳን ደስ አለን።

Read More

የሀገረ ስብከቱ ሁለተኛ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ

ከነሐሴ ፳፯ እስከ ነሐሴ ፳፰ ፳፻፲፬ ዓ/ም / Sept 2 & 3 2022 በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላስ ቬጋስ የተደረገው የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ስብሰባ መግለጫ፤

የሀገረ ስብከቱ የመጀመሪያ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ

ከሚያዝያ ፬ እስከ ሚያዝያ ፭ ፳፻፲፩ ዓ/ም / April 12-13 2019 በመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳንሆዜ ካሊፎርኒያ የተደረገው የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ስብሰባ መግለጫ፤

bottom of page